Ali Zegeye

Ali Zegeye Poems

የዘመናት ክስተት የምድር ሠማያት ቁጢት ሰብስቦ
ከጨለማ ንጋት የጊዜን አውታር ከላይ ቤት ስቦ
ከአፍሪቃ ኤሲያ ላንቃ ከዐባይ ቀይ ባሕር ልሳን
ከሥነፍጥረት ሕገ-ኑባሬ ከነሉሲ ቀዳሚ ድርሳን
...

Democracy the vital force FOR the civilized life

The alternative worthy remark of our strive
...

The Best Poem Of Ali Zegeye

Let The Knot Be One / ቋጠሮው አንድ ይሁን

የዘመናት ክስተት የምድር ሠማያት ቁጢት ሰብስቦ
ከጨለማ ንጋት የጊዜን አውታር ከላይ ቤት ስቦ
ከአፍሪቃ ኤሲያ ላንቃ ከዐባይ ቀይ ባሕር ልሳን
ከሥነፍጥረት ሕገ-ኑባሬ ከነሉሲ ቀዳሚ ድርሳን
ባህላዊ ፋና ከትናንት ዘርማንዘር
የሕይወት እንቆቅልሽ ትውፊት ሲመነዘር
የእስልምና ክርስትና ልዕልና ጣመራ ደሴት
የነገ አፍሪቃ አንድነት ሕብረቀለም ዕሴት
በዋቢ መዛግብት ዜና መዋዕል ሲዘከር ሲነገር
የሰው ዘር መነሻ ምድረ ቀደምት አገር
ኢትዮጵያ ታበጽህ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር የሚል ቀሚስ ለብሳ
በእናትነት የሞራል ቅርስ ብቅ ስትል ተመልሳ
ልጆቿን እንደሙሴ በብርሐን ዘንግ የምትመራ
ኢትዮጵያ ነች እንላለን የአፍሪቃ አንድነት ባለአደራ፡፡

መለኮታዊ ረቂቅ ምሥጢር እትብቷ ጋር የቋጠረች
በጸሎቷ ምሕዋር የተሸከረከረች
በሥነልቦና ተሐድሶ ቀና ብላ የተናገረች
የጀግኖቿ ጀግኒት አገሬ ነበረች፡፡
እነደ ሱፍ አበባ ወደ ፀሐይ ዞራ ስታበራ
በቬሎ ክብር ተሞሽራ የዘር ሐረግ ስታፈራ
ዘመናት ወራቱ ሕዋውም ነፋሱ
ከርሷ ጋር ተሰደው ለፍቅር ለሠላም አብረዋት ተነሱ
ከሆሜር ሄሮድስ መጽሐፈ ሔኖክ የታሪክ ትዝታ ጠልፎ
ከበርበራ እስከ ቀይ ባሕር ትዝብት አሰልፎ
አማራ ኦሮሞ ትግሬ- -ሱማሌ አደሬ- -ጉጂ ወላይታ
ሁሉም ብሔረሰቦች እንዲቋደሱ በአንድ ገበታ
ለዲሞክራሲ ሠርገኛ ጥሬ ለምድር ትንሳኤ
በሲኖዶስ መጅሊሰል አእላ- -ልጆቿን ኳኩላ- -ለፍትሕ ርትዕ ገብታለች ሱባኤ
"|ተዘወሪ መኪና ተዘወሪ- -ሸዋን አስመራ ሆየኑ መዛወሬ"
የሚል ዐርማ አንግተው
በነጣይቱ ወንፊት እብቁን ለይተው
ሲቲና አለውያ ማርያም አስመረይቲ የእናት ጽዋ ሞልተው
በዐድዋ ድል ተነቃቅተው ትግል የጀመሩት
ቅኝ ገዢን በሰፈረው ቁና ልኩን የሰፈሩት
የጀግና ልጅ ልጆች ከታሪክ ሠገነት
ሳለኝ እንዲወርዱ ለፍቅር አንድነት
ምቱ ነጋሪቱ በዐብይ ለማ ገዱ ደመቀ
ቀይ ባሕር ደራሽ ምንጭ አፈለቀ
ብለው ምንአለበት - - በአገር ልጅ አንደበት፡፡

የሚታየውን የግንብ አጥር ጀርመኖች ሲያፈርሱ
ኢትዮጵያና ኤርትራ ስውሩን ኬላ ሲደረምሱ
የነጻነት ዕኩልነት የሕይወት ዳግም ምሕንድስና
መብትና ግዴታ መስፈርት ሚዛናዊ ልግስና
ለዐለም ሠላም አዲስ ተምሳሌት
የታሪክን ቅንቅን አራግፎ ብቅ ሲል በስሌት
የኢትዮጵያ ዐየር መንገድ በሠንደቁ ደምቆ
ዐየር በዐየር ሲዋኝ የፍቅር የሠላም መቀነቱን ታጥቆ
አዲስ አበባ አስመራ ዐይን በዐይን ሲተያዩ
ከሕሊና በላይ መሬት ምን ተሰማት ምን አለ ሠማዩ፡፡

የናፍቆት ሙዚየም መሠረቱ ሲገነባ
ወገን ተፍለቅልቆ ሲወጣ ሲገባ
ለገፀ በረከት የፍቀር ጮራ ሥዕል ይጀመር
ምሥራቅ አፍሪቃም እንደጎሕ ፀዳል ቀድማ ትደመር፡፡

የአዲስ አበባ ቢኮሎሮማ ፀአዳ አስመራ
በዐደይ ዘንባባ ንብ ዕርግብ ቋንቋ ሲወራ
ኢትዮጵያ የሚል ስም ለሴት ልጆቻቸው
ይሰጡ የነበሩት ኤርትራውያን ናቸው፡፡
ጎንደር ወሎ ትግሬ ኤርትራ እትብቱን የቋጠረ
ለምሥክርነት የወንዜው ሊሻን ልጅ ተከዜም ነበረ፡፡

ዮናስና በረከት የፅንስ ጌጦቿ ጠፍተዋት ተጨንቃ
እናት ስትጣራ የምድር ሠማይ ጎራ ዘልቃ
የገደል ማሚቶ ሳይቀር አብሮ ጮሖ ሲያስተዛዝናት
ስለ አብርሐም ልጆች እሮሮ ሰምተናል በጽናት፡፡

የነ አማን አንዶም - - አብርሐም ደቦጭ ሞገስ አስገዶም - - የዘርዐይ ደረስ መንፈሥ የጀግንነት ወኔ
ትውፊቱን ሲያደራ በሕልሜም በውኔ
ዐርማቸውን የሚያነሳ ብቅ የሚል መሰለኝ
የዐድማስ ሕሊና ስድስተኛው ሕዋስ በኢንተርኔት ነገረኝ፡፡

የጭቁኖች ድል ዐድዋ ተወልዶ ቀይ ባሕር አድጎ
ሰርጅቷልና በደሜ ሰርጎ
ባለአደራ ካፒቴኖቹየኖህን መርከብ ተውሳችሁ
ከቀይባሕር እስከ በርበራ ወገን አሳፍራችሁ
ሥጋችን፣ ደማችን፣ ነፍሳችን፣ አንድ ነው ብላችሁ
ችቦ ለኩሱና ወደ እናታችሁ ተመለሱ
በሉሲ ዘፈን ላይ ሠላምን አንግሡ፡፡

ጃሌ ዐብይ መገርሳ፣ አቦይ ኢሳያስ ወዴ አፎይ
ለአገር ወገን ቋሚ ሽልማት የዘወትር እፎይ
በሥነ ልቦና ላቦራቶሪ ተደመሩና
የገፀ ሒሣብ አንብባችሁ ሥሩ ወደ እኛ ዙሩና፡፡

የአፍሪቃ ፍትሕ ሪፐብሊክ ዘንግ የማር አገዳ
ቃናው እንዲቀመስ የኦሮሞ ገዳ
ታሪክን ከምንጩ በሰባት ቅመም ከሽናችሁ
በእማዬ ሸክላ ድስት ያገሬን ዶሮ ወጥ ሥሩት እባካችሁ፡፡

መለኮታዊ ብራናዎች ፍቅር የሚያስተምሩት
ትሩፋት ነውና ልቦና ውስጥ የሚዘሩት
በዘመነ ትናንትና የጉቦን ቫይረስ ነቀርሳ
ሥሩ እንዲነቀል በእውነት ጦር ምሳ
የመካ ሙስሊም ሙስሊማት ስደተኞችን በሠላም የተቀበለች
ክርስትናን በቅዳሴ ውዳሴ ቅኔ የኳለች የዳረች
የእናት አባት ጠረን የዐየር ጠባይ የሞራል ውርስ
ከትውልድ ትልድ ተሸጋግሮ እራስ ጓዳ እንዲደርስ
በድንበር ዘለል ሤራ ጠነሳሸ አጋፋሪ
በስማ በለው ፍርፋሪ ነውጥ አቀናባሪ
በልጆቿ ንቃተ ሕሊና ተፅዕኖ መደናበር
ታሪኳ እነዳየከስም ቅሰሟ እንዳይሰበር
ነቅታችሁ ታጥቃችሁ ለልማት ተነሱ
የወቅቱን ፋና አብርታችሁ ወደ እውነት በር ተመለሱ፡፡

የትናንት ኢትዮጵያ ባሕር የዛሬ አትላንቲክ ውቅያኖስ
በውኃ ሙዚየም ስሙ አጥልቋልና የሐበሻን በርኖስ
ከዳአማት አክሱማዊት ትውፊት ቅብብሎሽ
ከኖላውያን፣ ሴማውያን፣ ኩሻውያን፣ ስብጥር ጥሎሽ
የዐባይ ሥልጣኔ ክንዋኔ ቀዳማዊ ተክለ ሰውነት
የምድረ ቀደምት አገር ውበት ብቅ እንዲል በአእምሮ ስበት
የሕይወት መሐንዲስ ጠቢብ የአንዲት ነፍስ አንጣሪ
የዐለማት ንጉሥ የጊዜ ባለቤት ኃያሉ ፈጣሪ
ምድር ሠማያትንበቃልኪዳን ቀለም እያሳመረ
የእውነት ዕምነትን ሐረግ ፍቅር ሠላም ጋር እያጣመረ
የነፍሰ ነባቢት - - ሥጋዊ ግፊት - - ቱሱልሱሉ እንዲሰምር
ሥነ ልቦናችን በአሀዱ ብሥራት አብሮን እንዲዘምር
ለአላህ እግዜር አንድዬ! ለሙሉ በኩሉሄ
በስባኤ ክህሎት - - በዱአ በጸሎት እላለሁ ኤሎሄ፡፡

"ቋጠሮው አንድ ነው" ካልኳት መጽሐፌ
ከግዞተኛዋ ሥነ ቃል ጠልፌ
በለምለም ቅኔ ቤት በምኞት አክናፌ
ከጣይቱ አዲስ አበባ ሳባ በወፍ በረር አስመራ ገብቼ
የቀይ ባሕር ሸጋን ዳህላክን ጎብኝቼ
የሠላም ቄጤማ የዕርግብ ዕንቁጣጣሽ ዘንባባ ሰጥቼ
ዐደይ አዲ ጀጋኑ - - ዘነበች ከመልአኪ - - ከሚለው ክራሬ
ትዝታ አሰምቼ ለትብለጽ መአሬ
ፀፀረት ማይጨሆት አባሻውል ሔጄ
ከውብ ፊያሜታ፣ ዳንኪራ ሳለኝ እስክስታ ወርጄ
ከሳሆ-ቢለኗ ከበኒ አሚሯ- - ከጥርሰ ወተቷ - - ከፊተ ፍንጭቷ- -የሁለመናዬ
ከአካለ ጉዛይ ሐማሴን ሠራዬ
ከሠሜኗ ኮከብ ኮከቤን ቆጥሬ
በሹሩባ ገዳም ዐይኔን ባይኗ አስሬ
ያይን ራብ እንዳላይ የአይን ኩሏ ሆኜ
ሳቅን ከነጣዕሙ በከንፈሯ ለዛ ሲፈካ መዝኜ
ከትንሳኤ በፊት እስትንፋስ ቢያቀምስኝ
የታሪክ መለከት ሱራፌል ቢያውሰኝ
ዘርዐይ ደረስን አሉላን ቀስቅሼ - - መልዕክቴን አድርሼ - -
የዘመድ ጥል የሥጋ ትል ብዬ - - ፍቅርን አሸምግዬ - - ዘመድ ከዘመዱ
አየቆረጥ ብዬ እትብቱ ገመዱ
ምጽዋ እየዋኘሁ - - አዲስ አበባን ባየሁ!
ብለው ምን አለበት - - ለታሪክ አንድነት
የፅን ወርቅ ሉል - - የሠማይ ትሩፋት ሠንደቅ ምልክቷ
ቋጠሮው አንድ ይሁን የዘር መቀነቷ
ብለው ምን አለበት በግጥም ጉባኤ
ለእማማ በረከት ለአገሬ ትንሳኤ፡፡
21/12/2010

Ali Zegeye Comments

Close
Error Success