ስትራመድ፡
ቀሚሷ
ያጎላው
ውበት፡
የወገቧ ቅጥነት
የዳሌዋ ኩራት
የሽንጧ ዳንሴነት
ያዜማል፡፡
መንገደኛው፡
ባይኑ ይሰማታል
ባይኑ ይስማታል፡፡
ስትራመድ፡
በራስ መተማመን ምድርን አስጨንቃ
ባለም በርሷ መፍዘዝ ከራሷ ጋር ስቃ
ተመልካች ፈገገ ውበቷን ለመቅሰም
ይታተም ይመስል ፈገግታዋ በሰም፡፡
ስትስቅ፡
ከጥርሷ ከጉንጯ
ካይንና ግንባሯ
ዕልፍ ፀሐይ ሠርቋል
ልዩ ሙቀት ያለው ከምሽት ጀንበሯ፡፡
ስትራመድ፡
ከቁብ የማትቆጥረው አያሌ ተመልካች
በዘለለት ኑሮ የነበረ ታካች
ልቡን ይሞርዳል ባይኗ የምስራች፡፡
ዳር ቆሜ ሳስተውል ነገሩን ባንክሮ
ይሔ ሁሉ ወጣት እሷን የሚያይ ዞሮ
ሻማ ሊሠራ ነው ከፀሐይ ቆንጥሮ
ገጿን የሚሞቀው ከጀንበሯ ቆጥሮ፡፡
This poem has not been translated into any other language yet.
I would like to translate this poem