ቀለል ያለ ጊዜ ጠነን ያለ ዘመን
ዐውሎ ያልጎበኘው ተሳቢ ሙሉ ዐየር
ቅርዘትም ጡዘትም ያልሸመቁት ቀዬ
አሳሪም ታሳሪም ያላወሩት ዘዬ
ቀለል ያለ ወግ ከንፈር ግጥም ሳቅ
ቀለል ያለ ስም ለጥሪ ማይርቅ
ቀለል ያለ ልብስ 'ማይከብድ ገላ
ቀለል ያለ መልክ የማይጣራ
ያልጋመ ቀለም ብሌን ያልናኘ
ዐደይ ቅብ ፍካት ሠርክ ያልተገኘ
ያልጮኸ ብርሐን ዐይን ያልወጋ
ያልጨለመ ያልተዘጋ
ጠነን ያለ ወዝ ከቶ ያልተብጫጫ
እጅግም ሳይፈዝ እንደ ግራጫ
ግማሽ ጠርሙስ ወይን ያልተተፋ
ግማሽ እንጀራ ያልቆነጠጠ
ለወግ የሚተርፍ ያላጠጠ
ቀለል ያለ ልብ ለጸብ ጥላቻ
እጅግ ያልቆመ ለፍቅር ብቻ
ስክን ያለ ርምጃ የተገራ መንገድ
ቀለል ያለ ጽሑፍ ለንባብ የማይከብድ
ልዝብ አንደበት እሳት ያልላሰ
ያልተለጎመ ያልተኮፈሰ
ምጥን ቁመና
ደልዳላ ገላ
|ያልገላወደ ያልመሰረ
ያልተንጠረበበ ያልተጠረበ
ያልሰባ ያልተላገ|
ልከኛ ዕውቀት ያልከረረ - መንገድ ያልወጣ
ወላንሳ ጠባይ ያልቀለለ - ካሉት ያልታጣ
ታዛዥ ሥሜት የተገራ
ካጋር ንበት የተሠራ
ሣር ለበስ ቅያስ በቅርብ የቀና
ግን የተሟሸ በስክን ዳና
እስኪ ጠቁሙኝ መልካም ጎዳና
ከሕልሜ ሚያደርስ ያለሙን ቃና፡፡
This poem has not been translated into any other language yet.
I would like to translate this poem