ስሜን አጠልሽታችሁ፣
ያልሆንኩትን ፈጥራችሁ፣
ብትሠርዙኝ ተባብራችሁ፣
ለዋውሳችሁ ብታጎድፉኝ፣
ብትረጋግጡኝ ብታቆሽሹኝ፣
እኔ እንደሁ ዕምቢኝ ባይ ነኝ።
አለሁ።
እንደ አቧራ ብንን እያልሁ
እነሣለሁ።
ጥንካሬን የተላበሰ ማንነቴ፣
ሊያግባባን ሲገባ አንደበቴ፣
ሊያስከብረኝ ሲገባ ኩራቴ፣
ራሴን በሥርዓት መግራቴ፣
ለምን ይሆን ማራቁ ማስናቁ?
እንደ ፀሐይቱ እንደ ጨረቃይቱ፣
ሳላዛንፍ ወቅት ጠብቄ የምገኝ፣
ወደ ከፍታ በሚወስድ ተስፋ፣
ተመልቼ ተመክቼ በደረሰብኝ ሳልደፋ፣
እቆማለሁ።
እንዲያውም እተምማለሁ።
ድፍት ብዬ ብቀር ይሻል ነበር?
እንደ ሸህላ ስብርብር?
መቋጫ በሌለው ዋይታ ተዳክሜ፣
መንፈሴ ላሽቆ ሰውነቴን ጥዬ ፣
አንገቴን አቀርቅሬ ዓይኖቼን ሰብሬ፣
ይበቃል ብያለሁ።
ተነሥቻለሁ።
የህይወት ሚስጥር እንደተገለጠላት፣
ሁሌ እንዳማረባት ሁሌ እንዳማረላት፣
ተጫዋች ፍልቅልቅ ሳቂታ ናት።
ይህ ሁሉ ለምን ረበሻችሁ?
ለመቀበል የተቸገራችሁ?
ድራሼን ለማጥፋት፣
እንዲያው ነው የምትደክሙት፣
የምትወረውሯቸው አልጣሉኝ፣
ጥላቻችሁ አልገደለኝ፣
ዓይኖቻችሁ አላሟሙኝ፤ አለሁኝ።
እንዳየር እናኛለሁ።
አለሁ።
ባላዎቼ መስካሪ፣
የሴትነት ወጌን አብሣሪ፣
አኳኋኔ ስሜትን ኮርኳሪ።
ዕንቁ አፍላቂ መምሰል፣
ማስደመም ማስደነቅ ሲችል፣
መብሰክሰካችሁ ጭራሽ መናደዳችሁ!
ደግም አይደል።
ተዳፍኖ የተረሣ ከመሰለ የታሪክ ጠባሳ፣
ገላልጬ ብቅ ብያለሁ።
አለሁ።
በሰቆቃ በሥቃይ በተገነባ የትላንት ማንነት፣
ይኸው ገነንሁበት።
እንደ ነውጠኛው ባሕር፣
የሚገለባበጠው ማዕበል በተነሣ ቁጥር፣
አኮበኩባለሁ።
አረገርጋለሁ።
እላወሳለሁ።
ባሳለፍሁት ላይ አዲስ አሻራ እፈጥራለሁ።
እነዚያን የመከራ የጨለማ የፍርሃት ጊዜያት፣
አውልቄ ጥዬ፤ አንቆ የያዘኝን ሠንሠለት፣
ያለፉቱ ቀደምቶቹ ባወረሱኝ መሠረት፣
ስሸጋገር በዕርግጠኝነት ወደ ብራው፣
ለተገፋው ለተደፋው ለተረገጠው ለከፋው፣
የማበሥረው
የማስረክበው
የማወርሰው፣
እነዚህን ነው
ህልም! ! ! ! !
ተስፋ! ! ! ! !
ስንቅ! ! ! ! !
ራሴን አድርጌ ታላቅ!
አሳያለሁ! ! ! ! ! ! ! ! ! !
እመራለሁ! ! ! ! ! ! ! ! !
አለሁ! ! ! ! ! ! ! ! ! ! ! !
እኖራለሁ! ! ! ! ! ! ! ! ! !
የካቲት 25 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት።